መክፈቻ
እዚህ ምንም ነገር አይከሰትም። ምንም ነገር አይስተካከልም፣ ምንም ነገር አይፈርስም። ምንም ትርጓሜ አይመጣም። ምንም መደምደሚያ። ይህ በአንድ ወቅት ድምፆች የነበሩ ቃላት ክር የተፈታ ጫፍ ነው። በአንድ ወቅት በዓለም እዚህና እዚያ፣ በኅዋ በአንዲት ጥግ፣ ወይም ምናልባት በሰው ምናብ በአንዲት ጥግ ብቻ ያስተጋቡ ድምፆች። አሁን፣ እነዚህ መስመሮች በዓይኖችህ ፊት ሲያልፉ፣ የእነዚያ ድምፆች ኃይል ከደበዘዘ ብዙ ጊዜ ሆኖታል፤ በገጹ ላይ የቀረው የእነርሱ ምናባዊ አሻራ ብቻ ነው። ሁሉም ጸጥ ብለዋል። ድምፆቹ ሁሉ፣ ምናልባትም ያ ዓለም ሁሉ ከሰዎቹ ጋር። ምናልባትም እነዚህን ድምፆች በወረቀት ላይ ያሰፈረው አእምሮ እንኳ ትንፋሽ ካልሳበ ብዙ ጊዜ ሆኖት ይሆናል። ልክ ይህች ቅጽበት — ይህን ዓረፍተ ነገር ያነበብክባት — እንዳለፈች፣ የዚህ መጽሐፍ ቅጽበቶች ሁሉ አልፈዋል። እዚህ ባይመዘገቡ ኖሮ በዓለም ክስተቶች ትኩሳት በተሞላ ጉምጉምታ ውስጥ ይጠፉ የነበሩ ቅጽበቶችና ምስሎች። የተመዘገቡትም በእኔ ዓለምና በአንተ ዓለም መካከል ድልድይ ይሆኑ ዘንድ ነው። እነዚህን ዓረፍተ ነገሮች በምጽፍባት ቅጽበት ካለው ከእኔ ዓለም፣ ልታነባቸው በምትቀመጥባት ቅጽበት ወዳለው ወደ አንተ ዓለም የሚዘረጋ ድልድይ። እኔ ከዚህ ወገን የቃላቱን ክር እፈታለሁ፤ አንተ ደግሞ ከዚያኛው ወገን ትሰበስባቸዋለህ። ልክ በልጅነታችን፣ ማማን የአሮጌ ልብሶችን የሱፍ ክር ስትፈታ እኛ ክሩን ይዘን የሱፍ ክሩ እንዳይከመር በቤቱ ውስጥ እንዞር እንደነበረው። ምናልባት የአንተ ትውልድ ከዚያ የሱፍ ክር ዓለም ጥቂት ዓመታት በኋላ መጥቶ ይሆናል፤ ግን አስብ፦ በአንድ ወቅት፣ በዓለም በሆነ ጥግ፣ የልጆች ጨዋታ እንዲህ ነበር። አሁን እኔ የቃላቱን ክር እፈታለሁ፤ አንተ ደግሞ አንሥተህ ወደ ራስህ ዓለም ውሰዳቸው፣ እዚህ፣ በእኔ ዓለም፣ እንዳይከመሩ።